1ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ፦
2“ነፍሴን የምትነዘንዙ፥ በቃልስ የምታደቅቁኝ እስከ መቼ ነው?
3ይኸው ስትሰድቡኝ አሥር ጊዜ ነው፤ ስታሻክሩኝም አላፈራችሁም።
4በእውነትም የሳትሁ እንደ ሆነ፥ ስሕተቴ ከእኔ ጋር ትኖራለች።
5በእውነትም ብትጓደዱብኝ፥ መዋረዴን በእኔ ላይ ብትከራከሩ፥
6እንግዲህ እግዚአብሔር እንደ ገለበጠኝ፥ በመረቡም እንደ ከበበኝ እወቁ።
7“እነሆ፥ ስለ ተደረገብኝ ግፍ ብጮኽ ማንም አይመልስልኝም፤ አሰምቼም ብጠራ ፍርድ የለኝም።
8እንዳላልፍ መንገዴን ዘግቶታል፥ በጎዳናዬም ጨለማ አኑሮበታል።
9ክብሬን ገፈፈኝ፥ ዘውዴንም ከራሴ ላይ ወሰደ።
10በዚህና በዚያም አፈረሰኝ፥ እኔም ሄድሁ፤ ተስፋዬንም እንደ ዛፍ ነቀለው፤
11ቍጣውንም አነደደብኝ፥ እንደ ጠላቱም ቈጠረኝ።
12ሠራዊቱ አብረው መጡ፥ መንገዳቸውንም በላዬ አዘጋጁ፥ በድንኳኔም ዙሪያ ሰፈሩ።
13“ወንድሞቼን ከእኔ ዘንድ አራቀ፥ የሚያውቁኝም አጥብቀው ተለዩኝ።
14ዘመዶቼ ተቋረጡ፥ ወዳጆቼም ረሱኝ።
15ቤተ ሰቦቼና ሴቶች ባሪያዎቼ እንደ መጻተኛ ቈጠሩኝ፤ በዓይናቸውም እንደ እንግዳ ሆንሁ።
16ባሪያዬን ብጠራ፥ በአፌም ባቈላምጥ አይመልስልኝም።
17ሚስቴ እስትንፋሴን ጠላች፥ የእናቴም ማኅፀን ልጆች ልመናዬን ጠሉ።
18ሕፃናቶች እንኳ አጠቁኝ፤ ብነሣም በእኔ ላይ ይናገራሉ።
19አማካሪዎቼ ሁሉ ተጸየፉኝ፤ እኔ የምወድዳቸው በላዬ ተገለበጡ።
20አጥንቴ ከቁርበቴና ከሥጋዬ ጋር ተጣበቀ፤ ድድ ብቻ ቀርቶልኝ አመለጥሁ።
21“እናንተ ወዳጆቼ ሆይ፥ ማሩኝ፤ የእግዚአብሔር እጅ መትታኛለችና ማሩኝ።
22ስለ ምን እናንተ እንደ እግዚአብሔር ታሳድዱኛላችሁ? ከሥጋዬስ ስለ ምን አትጠግቡም?
23“ምነው አሁን ቃሌ ቢጻፍ! ምነው በመጽሐፍ ውስጥ ቢታተም!
24ምነው በብረት ብርና በእርሳስ፡ በዓለቱ ላይ ለዘላለም ቢቀረጽ!
25እኔን ግን የሚቤዠኝ ሕያው እንደ ሆነ፥ በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንዲቆም፥
26ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ፥ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ።
27እኔ ራሴ አየዋለሁ፥ ዓይኖቼም ይመለከቱታል፥ ከእኔም ሌላ አይደለም። ልቤ በመናፈቅ ዝሎአል።
28“በእውነት፦ ‘እንዴት እናሳድደዋለን? የነገሩ ሥር በእርሱ ዘንድ ተገኝቶአል፡’ ብትሉ፥
29ፍርድ እንዳለ ታውቁ ዘንድ፡ ቍጣ የሰይፍን ቅጣት ያመጣልና፡ ከሰይፍ ፍሩ።”