ትንቢተ ኤርምያስ 16

AMHNIVአማርኛ21 ጥቅሶች4:45 አዳምጥ
አዳምጥ 4:45 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤

2“በዚህ ስፍራ ሚስት አታግባ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም አይኑሩህ፤”

3በዚህች ምድር ስለሚወለዱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች፣ እንዲሁም ስለ እናቶቻቸው ስለ አባቶቻቸው እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤

4“በአደገኛ በሽታ ይሞታሉ፤ አይለቀስላቸውም፤ አይቀበሩም፤ በምድርም ላይ እንደ ጒድፍ ይጣላሉ። በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ፤ ሬሳቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናል።”

5እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ “በረከቴን፣ ፍቅሬንና ምሕረቴን ከዚህ ሕዝብ አርቄ አለሁና፤ ልቅሶ ወዳለበት ቤት አትግባ፤ ታለቅስና ታዝንም ዘንድ አትሂድ” ይላል እግዚአብሔር።

6“ታላላቆችና ታናናሾች በዚህች ምድር ይሞታሉ፤ አይቀበሩም፤ አይለቀስላቸውም፤ ሰውነቱን የሚቧጥጥላቸው፣ ጠጒሩንም የሚላጭላቸው አይገኝም፤

7ሐዘንተኞችን ለማጽናናት የእዝን እንጀራ የሚያመጣ አይኖርም፤ አባትም ሆነ እናት የሞተባቸውንም ለማጽናናት መጠጥ የሚያቀርብ አይገኝም።

8“ከእነርሱ ጋር ተቀምጠህ ለመብላትና ለመጠጣት ድግስ ወዳለበት ቤት አትግባ፤

9የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘እነሆ፤ በዐይናችሁ ፊት፣ በዘመናችሁም የደስታና የሐሤት ድምፅ፣ የሙሽራውንና የሙሽራዪቱን ድምፅ ከዚህ ስፍራ አስወግዳለሁ።’

10“ይህን ሁሉ ለዚህ ሕዝብ በምትነግርበት ጊዜ ሰዎቹ፣ ‘እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ታላቅ ጥፋት በእኛ ላይ ለምን ዐወጀ? በደላችንስ ምንድን ነው? በአምላካችንስ በእግዚአብሔር ላይ የሠራነው ኀጢአት ምንድን ነው?’ ብለው ቢጠይቁህ፣

11እንዲህ ትላቸዋለህ፤ ‘አባቶቻችሁ እኔን ስለተውኝ ነው’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘ሌሎችን አማልክት በመከተል፣ ስላገለገሏቸውና ስላመለኳቸው ነው፤ ትተውኝ ኰበለሉ፤ ሕጌንም አልጠበቁም።

12እናንተም ደግሞ ከአባቶቻችሁ የባሰ ክፉ ነገር አድርጋችኋል፤ እያንዳንዳችሁ እኔን በመታዘዝ ፈንታ የልባችሁን ክፋት ምን ያህል በእልኸኝነት እንደምትከተሉ ተመልከቱ።

13ስለዚህ ከዚህች ምድር አውጥቼ፣ እናንተም ሆነ አባቶቻችሁ ወደማታውቁት ምድር እጥላችኋለሁ፤ ምሕረትንም አላደርግላችሁምና በዚያ ሌሎችን አማልክት ቀንና ሌሊት ታገለግላላችሁ።’

14“ስለዚህ ሰዎች፦ ‘እስራኤላውያንን ከግብፅ ምድር ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን’ ብለው ከእንግዲህ የማይምሉበት ዘመን ይመጣል” ይላል እግዚአብሔር፤

15“ነገር ግን፣ እስራኤላውያንን ከሰሜን ምድርና እነርሱን ከበተነባቸው ከሌሎች አገሮች ሁሉ ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን!’ ይላሉ፤ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋቸው ምድር እመልሳቸዋለሁና።

16“አሁን ግን ብዙ ዓሣ አጥማጆችን እልካለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “እነርሱም ያጠምዷቸዋል። ከዚያም በኋላ ብዙ አዳኞችን እሰዳለሁ፤ እነርሱም ከየተራራው፣ ከየኰረብታው ሁሉ ከየዐለቱም ስንጣቂ አድነው ይይዟቸዋል።

17ዐይኔ በመንገዳቸው ሁሉ ላይ ነው፤ በፊቴ የተገለጡ ናቸው፤ ኀጢአታቸውም ከዐይኔ የተሰወረ አይደለም።

18ምድሬን በድን በሆኑ አስጸያፊ ጣዖቶቻቸው ስላረከሱ፣ ርስቴንም በአሳፋሪ ነገሮች ስለሞሉ፣ ላደረጉት በደልና ኀጢአት ዕጥፍ እከፍላቸዋለሁ።”

19ብርታቴና ምሽጌ፣ በመከራ ቀን መጠጊያዬ የሆንህ እግዚአብሔር ሆይ፤ አሕዛብ ከምድር ዳርቻ፣ ወደ አንተ መጥተው እንዲህ ይላሉ፤ “አባቶቻችን ለአንዳች ነገር ያልረቧቸውን ከንቱ ጣዖቶች፣ የሐሰት አማልክትን ወረሱ።

20ሰዎች ለራሳቸው አማልክትን ያበጃሉን? ያደርጉ ይሆናል፤ እንዲህ ዐይነቶቹ ግን አማልክት አይደሉም።”

21“ስለዚህ አስተምራቸዋለሁ፤ ኀይሌንና ታላቅነቴን፣ አሁን አስተምራቸዋለሁ፤ እነርሱም ስሜ እግዚአብሔር፣ እንደሆነ ያውቃሉ።

ማብራሪያ

16:1-9 ነቢዩ አገሩ በጣም በቅርቡ እንደምትወድም የሚጠብቅ ሰው ሆኖ ራሱን መምራት አለበት። አሳዛኝ ጊዜያት በሚመጡበት ወቅት፣ ከጋብቻ፣ ለሙታን ከማዘን፣ እና ከደስታ መታቀብ አለበት። የእግዚአብሔርን እውነት ለሌሎች ለማሳመን የሚሹ፣ ራሳቸውን በመካድ እነሱ ራሳቸው በእርሱ እንደሚያምኑ ግልጽ ማድረግ አለባቸው። ሰላም፣ ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ፣ የቤተሰብም ሆነ የህዝብ፣ ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሔር ሥራ ሲሆን፣ ከርሱ ታላቅ ፍቅርና ምሕረት የመነጨ ነው። እርሱ ሰላሙን ከማንኛውም ሕዝብ ሲያነሳ፣ መከራ ይከተላል። አለበለዚያ ግዴታችን የሆኑ ነገሮችን መራቅ ተገቢ የሚሆንባቸው ጊዜያት ሊኖሩ ይችላሉ፤ ሁልጊዜም የዚህን ዓለም ደስታዎችና አሳቦች በጥብቅ ልንይዛቸው አይገባም።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6