ትንቢተ ኤርምያስ 11

AMHEVGአማርኛ22 ጥቅሶች4:18 አዳምጥ
አዳምጥ 4:18 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው።

2የዚህን ቃል ኪዳን ቃል ስማ፥ ለይሁዳም ሰዎች በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ተናገር፥

3እንደዚህም በላቸው፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከግብፅ አገር ከብረት ምድጃ ባወጣኋቸው ቀን ለአባቶቻችሁ ያዘዝሁትን የዚህን ቃል ኪዳን ቃል የማይሰማ ሰው ርጉም ይሁን፤ አልሁም፦ ቃሌን ስሙ፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ አድርጉ፤ እንዲሁም እናንተ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ።

5ይህም ዛሬ እንደ ሆነ ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር እሰጣቸው ዘንድ ለአባቶቻችሁ የማልሁትን መሐላ አጸና ዘንድ ነው። እኔም፦ አቤቱ፥ አሜን፡ ብዬ መለስሁለት።

6እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ ይህችን ቃል ሁሉ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ ተናገር፥ እንዲህም በል፦ የዚህን ቃል ኪዳን ቃል ስሙ አድርጉትም።

7አባቶቻችሁን ከግብፅ ምድር ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፥ በማለዳ ተነሥቼ እያስጠነቀቅሁ፦ ቃሌን ስሙ፡ በማለት አስጠንቅቄአቸው ነበር።

8እነርሱ ሁሉ ግን በክፉ ልባቸው እልከኝነት ሄዱ እንጂ አልሰሙም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም፤ ስለዚህ ያዘዝኋቸውን እነርሱም ያላደረጉትን የዚህን ቃል ኪዳን ቃል ሁሉ አመጣሁባቸው።

9እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ በይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም በሚኖሩ ዘንድ አድማ ተገኝቶአል።

10ቃሌንም ይሰሙ ዘንድ እንቢ ወዳሉ ወደ አባቶቻቸው ኃጢአት ተመለሱ፥ ያመልኩአቸውም ዘንድ እንግዶችን አማልክት ተከተሉ፤ የእስራኤል ቤትና የይሁዳ ቤት ከአባቶቻቸው ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን አፈረሱ።

11ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ሊያመልጡት የማይችሉትን ክፉ ነገር አመጣባቸዋለሁ፥ ወደ እኔም ይጮኻሉ፤ እኔም አልሰማቸውም።

12በይሁዳም ከተሞችና በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሄደው ወደሚያጥኑላቸው አማልክት ይጮኻሉ፤ ነገር ግን በመከራቸው ጊዜ ከቶ አያድኑአቸውም።

13ይሁዳ ሆይ፥ አማልክትህ እንደ ከተሞችህ ቍጥር እንዲሁ ናቸው፤ እንደ ኢየሩሳሌምም መንገዶች ቍጥር ለነውረኛ ነገር መሠዊያ፥ እርሱም ለበኣል ታጥኑበት ዘንድ መሠዊያ፥ አድርጋችኋል።

14አንተም ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ፤ ከመከራቸው የተነሣ ወደ እኔ በጮኹ ጊዜ አልሰማቸውምና ስለ እነርሱም ጩኸትና ልመና አታድርግ።

15ወዳጄ በቤቴ ውስጥ ምን አላት? ስእለት ወይም የተቀደሰ ሥጋ ክፋትሽን ከአንቺ ያስወግዳልን? ወይስ በእነዚህ ታመልጫለሽን?

16እግዚአብሔር ስምሽን፦ በመልካም ፍሬ የተዋበች የለመለመች የወይራ ዛፍ፡ ብሎ ጠራው፤ በጽኑ ዐውሎ ነፋስ ጩኸት እሳትን አነደደባት፥ ቅርንጫፎችዋም ተሰብረዋል።

17ለበኣልም በማጠናቸው ያስቈጡኝ ዘንድ ለራሳቸው ስለ ሠሩአት ስለ እስራኤልና ስለ ይሁዳ ቤት ክፋት የተከለሽ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ክፉን ነገር ተናግሮብሻል።

18እግዚአብሔርም አስታወቀኝ እኔም አወቅሁ፤ ሥራቸውንም ገለጥህልኝ።

19እኔም ለመታረድ እንደሚነዳ እንደ የዋህ በግ ጠቦት ሆንሁ፤ እነርሱም፦ ዛፉን ከፍሬው ጋር እንቍረጥ፥ ስሙም ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይታሰብ ከሕያዋን ምድር እናጥፋው፡ ብለው ምክርን እንዳሰቡብኝ አላወቅሁም ነበር።

20ኵላሊትንና ልብን የምትፈትን በቅንም የምትፈርድ አቤቱ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ ክርክሬን ገልጬልሃለሁና በእነርሱ ላይ የሚሆን በቀልህን ለይ።

21ስለዚህም፦ በእጃችን እንዳትሞት በእግዚአብሔር ስም ትንቢት አትናገር፡ ብለው ነፍስህን ስለሚሹ ስለ ዓናቶት ሰዎች እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ እቀጣቸዋለሁ፤

22ጎበዛዝቶቻቸው በሰይፍ ይሞታሉ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውም በራብ ይሞታሉ፤

23በምጐበኛቸውም ዓመት በዓናቶት ሰዎች ላይ ክፉ ነገር አመጣባቸዋለሁና ማንም ከእነርሱ የሚቀር የለም።

ማብራሪያ

11:1-10 እግዚአብሔር በፈቃደኝነት አለመታዘዝ ውስጥ እስከሚጸኑ ድረስ፣ ምክንያታዊ ለሆኑ ፍጥረታቱ በረከቶችን ለመስጠት ቃል አልገባም። ይቅርታና መቀበል ለሚያምኑ ሁሉ በነጻ ቃል ተገብቶላቸዋል፤ ነገር ግን ንስሐ ለመግባት፣ በክርስቶስ ለማመን፣ ከኃጢአትና ከዓለም ለመለየት፣ ራስን መካድንና የሕይወትን መታደስን ለመምረጥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የማይታዘዝ ማንም ሰው ሊድን አይችልም። በአጠቃላይ ሰዎች ስለ ትምህርቶች፣ ተስፋዎችና መብቶች ለሚናገሩ ያዳምጣሉ፤ ነገር ግን ግዴታዎች ሲጠቀሱ ጆሯቸውን አያዘነብሉም።

11:11-17 ክፋት ኃጢአተኞችን ያሳድዳል፣ በወጥመድም ውስጥ ያጠምዳቸዋል፣ ከእርሱም ራሳቸውን ነጻ ማድረግ አይችሉም። አሁን ግን፣ በመከራቸው ጊዜ፣ ብዙ አማልክቶቻቸውና ብዙ መሠዊያዎቻቸው ምንም አይጠቅሟቸውም። የራሳቸው ጸሎት የማይሰማላቸው እነዚያ ከሌሎች ጸሎት ጥቅም ሊጠብቁ አይችሉም።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6