ትንቢተ ኢሳይያስ 5

AMHNIVአማርኛ30 ጥቅሶች6:05 አዳምጥ
አዳምጥ 6:05 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ስለ ወዳጄ፣ ደግሞም ስለ ወይን ቦታው ልዘምር፤ ወዳጄ በለምለም ኰረብታ ላይ የወይን ቦታ ነበረው።

2መሬቱን ቈፈረ፤ ድንጋይንም ለቅሞ አወጣ፤ ምርጥ የሆነውንም ወይን ተከለበት። በመካከሉ መጠበቂያ ማማ ሠራ፤ የወይን መጭመቂያ ጒድጓድም አበጀ፤ ከዚያ መልካም ፍሬ ያፈራል ብሎ አሰበ፤ ነገር ግን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ።

3“እናንት በኢየሩሳሌም የምትኖሩና የይሁዳ ሰዎች ሆይ፤ በእኔና በወይኔ ቦታ መካከል እስቲ ፍረዱ።

4ከዚህ ካደረግሁለት በላይ ለወይኔ ቦታ ምን ሊደረግለት ይገባ ነበር? መልካም የወይን ፍሬ ያፈራል ብዬ ስጠብቅ ለምን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ?

5እንግዲህ በወይኔ ቦታ ምን እንደማደርግ ልንገራችሁ፤ ዐጥሩን እነቅላለሁ፤ ለጥፋት ይጋለጣል፤ ግንቡንም አፈርሳለሁ፣ መረጋገጫም ይሆናል።

6የማይኰተኰትና የማይታረም ጠፍ መሬት አደርገዋለሁ፤ ኵርንችትና እሾኽም ይበቅልበታል፤ ዝናብም እንዳይዘንብበት ደመናዎችን አዝዛለሁ።”

7የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር የወይን ቦታው የእስራኤል ቤት ነው፤ የይሁዳ ሰዎችም የደስታው አትክልት ናቸው። ፍትሕን ፈለገ፤ ነገር ግን ደም ማፍሰስን አየ፤ ጽድቅን ፈለገ፤ ነገር ግን የጭንቅን ጩኸት ሰማ።

8ስፍራ ለሌሎች እስከማይተርፍ፣ ቤትን በቤት ላይ በመጨመር፣ መሬትን ከመሬት ጋር በማያያዝ፣ ለብቻችሁ በምድር ተስፋፍታችሁ ለምትኖሩ ወዮላችሁ

9የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ጆሮዬ እየሰማ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “ታላላቅ ቤቶች ወና ይቀራሉ፣ የሚያማምሩም ቤቶች ኗሪ ያጣሉ።

10ከሩብ ጋሻ የወይን ቦታ አንድ የባዶስ መስፈሪያ ያህል የወይን ጭማቂ ብቻ ይገኛል፤ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ዘር ተዘርቶ አንድ የኢፍ መስፈሪያ እህል ብቻ ይሰጣል።

11የሚያሰክር መጠጥ ፍለጋ ማልደው ለሚነሡ፣ እስኪያነዳቸውም ወይን በመጠጣት ሌሊቱን ለሚያነጉ ወዮላቸ

12በግብዣቸው ላይ በገናና መሰንቆ፣ ከበሮና ዋሽንት እንዲሁም የወይን ጠጅ አለ፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ሥራ ቦታ አልሰጡም፤ ለእጆቹም ሥራ ክብር አላሳዩም።

13ስለዚህ ሕዝቤ ዕውቀት በማጣቱ ይማረካል፤ መኳንንቱም በራብ ይሞታሉ፤ ሕዝቡም በውሃ ጥም ይቃጠላል።

14ስለዚህ ሲኦል ሆዷን አሰፋች፣ አፏንም ያለ ልክ ከፈተች፤ መኳንንቱና ሕዝቡ ከረብሸኞቻቸውና ከጨፋሪዎቻቸው ጋር ወደዚያ ይወርዳሉ።

15ሰው ይዋረዳል፤ የሰው ልጅም ዝቅ ዝቅ ይላል፤ የእብሪተኛውም ዐይን ይሰበራል።

16የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ግን በፍትሕ ከፍ ከፍ ይላል፤ ቅዱሱም አምላክ ቅድስናውን በጽድቅ ይገልጻል።

17በጎችም በገዛ መሰማሪያቸው እንደሚሰማሩ ሆነው ይግጣሉ፤ የበግ ጠቦቶችም በባለጠጎች ፍርስራሽ ላይ ሣር ይበላሉ።

18ኀጢአትን በማታለል ገመድ ለሚስቡ፣ በደልንም በሠረገላ ማሰሪያ ለሚጐትቱ ወዮላቸው!

19በዐይናችን እንድናይ እግዚአብሔር ይቸኵል፤ ሥራውንም ያፋጥን፤ የእስራኤልን ቅዱስ፣ የእርሱን ዕቅድ እንድናውቃት ትቅረብ፤ ትምጣም ለሚሉ ወዮላቸው!”

20ክፉውን መልካም፣ መልካሙን ክፉ ለሚሉ ብርሃኑን ጨለማ፣ ጨለማውን ብርሃን ለሚያደርጉ፣ ጣፋጩን መራራ፣ መራራውንም ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው!

21ራሳቸውን እንደ ብልኅ ለሚቈጥሩ፣ በራሳቸውም አመለካከት ጥበበኛ ለሆኑ ወዮላቸው!

22የወይን ጠጅ ለመጠጣት ጀግኖች፣ የሚያሰክር መጠጥ ለመደባለቅ ብርቱ ለሆኑ ወዮላቸው!

23ጒቦን በመቀበል በደለኛን ንጹሕ ለሚያደርጉ፣ ለበደል አልባ ሰው ፍትሕን ለሚነፍጉ ወዮላቸው!

24ስለዚህ የእሳት ነበልባል ገለባን እንደሚበላ፣ ድርቆሽም በእሳት ጋይቶ እንደሚጠፋ፣ የእነርሱም ሥር እንዲሁ ይበሰብሳል፤ አበባቸውም እንደ ትቢያ ይበናል፤ የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን ሕግ ንቀዋልና፤ የእስራኤል ቅዱስ የተናገረውንም ቃል አቃለዋል።

25የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነዶአል፤ እጁን አንሥቶ መቶአቸዋል፤ ተራሮች ራዱ፤ ሬሳዎችም በመንገድ ላይ እንደተጣለ ጥራጊ ሆኑ፤ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ቍጣው ገና አልተመለሰም፤ እጁም እንደ ተነሣ ነው።

26ከሩቅ ያሉትን ሕዝቦች የሚጠራበትን ምልክት ያቆማል፤ ከምድር ዳርቻም በፉጨት ይጠራቸዋል፤ እነርሱም እየተጣደፉ በፍጥነት ይመጣሉ።

27በመካከላቸው ደካማና ስንኩል አይገኝም፤ የሚያንቀላፋና የሚተኛ አይኖርም፤ የወገባቸው መቀነት አይላላም፤ የጫማቸውም ማሰሪያ አይበጠስም።

28ፍላጻቸው የተሳለ፣ ቀስታቸውም የተደገነ ነው፤ የሠረገሎቻቸውም መንኰራኵሮች እንደ ዐውሎ ነፋስ ናቸው።

29ጩኸታቸው እንደ አንበሳ ነው፤ እንደ አንበሳ ደቦል ያገሣሉ፤ ያደኑትንም ይዘው ይጮኻሉ፤ ተሸክመውት ይሄዳሉ፤ የሚያስጥልም የለም።

30በዚያን ቀን እንደ ባሕር ሞገድ ይጮኹበታል፤ ማንም ወደ ምድር ቢመለከት፣ ጨለማንና መከራን ያያል፤ ብርሃን እንኳ በደመናዎች ይጋረዳል።

ማብራሪያ

5:1-7 ክርስቶስ የእግዚአብሔር የተወደደው ልጅ ሲሆን፣ የእኛም ተወዳጅ አዳኛችን ነው። ጌታ በእስራኤል ሕዝብ ላይ የነበረው እንክብካቤ የወይን እርሻ አስተዳደር ምሳሌ ተደርጎ ተገልጿል። ያለንበት ሁኔታ የሚሰጠን ምቹነቶች አንድ ቀን ይፈረድባቸዋል። እርሱም እጅግ ምርጥ በሆኑ የወይን ዛፎች ተከለ፣ እጅግ የላቀ ሕግ ሰጣቸው፣ ተገቢ የሆኑ ሥርዓቶችንም ደነገገ። ቤተ መቅደሱ እግዚአብሔር የመገኘቱን ምልክቶች የሰጠበት ግንብ ነበር። መሠዊያውንም አቆመ፣ መሥዋዕቶችም የሚቀርቡበትን ቦታ አዘጋጀ፤ በዚህም ሁሉ የጸጋ መንገዶች ተጠቁመዋል። እግዚአብሔር መብቶችን ከሚያጣጥሙት ፍሬ ይጠብቃል። መልካም ዓላማዎችና ጥሩ ጅማሬዎች መልካም ናቸው፣ ግን በቂ አይደሉም። የወይን እርሻ ፍሬ መኖር አለበት፤ ማለትም ከመንፈስ ጋር የሚስማሙ ሐሳቦችና ስሜቶች፣ ቃላትና ተግባራት።

እርሱም ክፉ ፍሬ አፈራ። የዱር ወይኖች የጠማማ ተፈጥሮ ፍሬዎች ናቸው። ጸጋ በማይሠራበት ቦታ፣ መበላሸት ይነግሣል። ነገር ግን ሃይማኖትን በሚናገሩትና የጸጋ መንገዶችን በሚያገኙት ላይ ያለው ክፋት በራሳቸው በኃጢአተኞች ላይ ይሆንባቸዋል። ከእንግዲህ ወዲህ የተለየ ሕዝብ አይሆኑም። ስህተቶችና ክፋቶች ያለ ገደብ ወይም ቁጥጥር ሲሄዱ፣ የወይን እርሻው አይከረከምም፤ ከዚያም ወዲያውኑ በእሾህ ይወረራል። ይህ ብዙ ጊዜ እግዚአብሔርን ለረጅም ጊዜ ሲቃወሙ ከኖሩት የእግዚአብሔር መንፈስ ሲርቅ፣ እንዲሁም ወንጌሉን ለረጅም ጊዜ ስም ካጠፉባቸው ስፍራዎች ሲወገድ ይታያል።

ማብራሪያው ተሰጥቷል። እግዚአብሔር ከሚጠብቀው የትሕትና፣ የየዋህነት፣ የፍቅር፣ የትዕግሥትና ዓለምን የመናቅ የወይን ፍሬዎች ይልቅ የትዕቢት፣ የቁጣ፣ የቅሬታ፣ የክፋትና እግዚአብሔርን የመናቅ የዱር ወይኖች ሲገኙ ለአንድ ነፍስ ያሳዝናል። ከመጸለይና ከማመስገን የወይን ፍሬዎች ይልቅ ደግሞ የመርገም እና የመሳደብ የዱር ወይኖች ሲገኙ ያሳዝናል። የዘላለም ሕይወትን እንድናገኝ በፍጹም ትዕግሥት ፍሬ እናፍራ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6