1እንግዲህ ወደ ዕረፍቱ ለመግባት የተሰጠው ተስፋ አሁንም የተጠበቀ ስለ ሆነ፣ ከእናንተ ማንም ለዚያ ሳይበቃ እንዳይቀር እንጠንቀቅ፤
2ለእነዚያ እንደ ተሰበከ ለእኛም ደግሞ የምሥራቹ ቃል ተሰብኮልናልና። ነገር ግን ሰሚዎቹ ቃሉን ከእምነት ጋር ስላላዋሐዱት አልጠቀማቸውም።
3እኛ ያመንነው ግን ወደዚያ ዕረፍት እንገባለን፤ እግዚአብሔርም፣ “ስለዚህ በቍጣዬ እንዲህ ብዬ ማልሁ፤ ‘ወደ ዕረፍቴ ከቶ አይገቡም’ ” ብሎአል። ይሁን እንጂ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የእርሱ ሥራ ተከናውኖአል።
4ስለ ሰባተኛውም ቀን በአንድ ስፍራ፣ “በሰባተኛውም ቀን እግዚአብሔር ከሥራው ሁሉ ዐረፈ” ብሎአልና።
5ቀደም ባለው ክፍል ደግሞ፣ “ወደ ዕረፍቴ ከቶ አይገቡም” ይላል።
6ወደ ዕረፍቱ ገና የሚገቡ አንዳንዶች አሉ፤ ቀድሞ የምሥራቹ ቃል የተሰበከላቸው ባለመታዘዛቸው ምክንያት ወደ ዕረፍት አልገቡም።
7ስለዚህ እግዚአብሔር፣ “ዛሬ” ብሎ እንደ ገና አንድን ቀን ወሰነ፤ ይህም ከብዙ ዘመን በኋላ በዳዊት በኩል፣ “ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ፣ ልባችሁን አታደንድኑ” ተብሎ ቀደም ሲል እንደ ተነገረው ነው።
8ኢያሱ ዕረፍትን ሰጥቶአቸው ቢሆን ኖሮ፣ ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረ ነበር።
9ስለዚህ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ገና ቀርቶለታል፤
10ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር ዕረፍት የሚገባ ሁሉ፣ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ፣ እርሱም ደግሞ ከሥራው ያርፋል።
11እንግዲህ ማንም የእነዚያን አለመታዘዝ ምሳሌ ተከትሎ እንዳይወድቅ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ።
12የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ ስለታም ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል።
13ከእግዚአብሔር ዐይን የተሰወረ ምንም ፍጥረት የለም፤ ስለ ራሳችን መልስ መስጠት በሚገባን በእርሱ ፊት ሁሉም ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው።
14እንግዲህ ወደ ሰማያት ያረገ ታላቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፣ እምነታችንን አጥብቀን እንያዝ።
15በድካማችን የማይራራልን ሊቀ ካህናት የለንምና፤ ነገር ግን እንደ እኛ በማንኛውም ነገር የተፈተነ ሊቀ ካህናት አለን፤ ይሁን እንጂ ምንም ኀጢአት አልሠራም።
16እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበልና በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ፣ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።