ትንቢተ ዕንባቆም 3

AMHEVGአማርኛ19 ጥቅሶች3:04 አዳምጥ
አዳምጥ 3:04 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1የነቢዩ የዕንባቆም ጸሎት በመዝሙር።

2አቤቱ፥ ዝናህን ሰምቼ ፈራሁ፤ አቤቱ፥ በዓመታት መካከል ሥራህን ፈጽም፤ በዓመታት መካከል ትታወቅ፤ በመዓት ጊዜ ምሕረትን አስብ።

3እግዚአብሔር ከቴማን፥ ቅዱሱም ከፋራን ተራራ ይመጣል። ክብሩ ሰማያትን ከድኖአል፥ ምስጋናውም ምድርን ሞልቶአል።

4ፀዳሉም እንደ ብርሃን ነው፤ ጨረር ከእጁ ወጥቶአል፤ ኃይሉም በዚያ ተሰውሮአል።

5ቸነፈር በፊቱ ይሄዳል፥ የእሳትም ነበልባል ከእግሩ ይወጣል።

6ቆመ፥ ምድርንም አወካት፤ ተመለከተ፥ አሕዛብንም አናወጠ፤ የዘላለምም ተራሮች ተቀጠቀጡ፥ የዘላለምም ኮረብቶች ቀለጡ፤ መንገዱ ከዘላለም ነው።

7የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ፤ የምድያም አገር መጋረጃዎች ተንቀጠቀጡ።

8በውኑ እግዚአብሔር በወንዞች ላይ ተቈጥቶአልን? ቍጣህ በወንዞች ላይ፥ መዓትህም በባሕር ላይ ነውን? በፈረሶችህና በማዳንህ ሰረገሎች ላይ ተቀምጠሃልና።

9በቃልህ እንደ ማልህ መቅሠፍትህን አወጣህ፤ ቀስትህንም ገተርህ፤ ምድርን ሰንጥቀህ ፈሳሾችን አወጣህ።

10ተራሮች አንተን አይተው ተጨነቁ፤ የውኃ ሞገድ አልፎአል፤ ቀላዩም ድምፁን ሰጥቶአል፥ እጁንም ወደ ላይ አንሥቶአል።

11ፍላጾችህ ከወጡበት ብርሃን የተነሣ፥ ከሚንቦገቦገውም ከጦርህ ፀዳል የተነሣ፥ ፀሐይና ጨረቃ በመኖሪያቸው ቆሙ።

12በምድር ላይ በመዓት ተራመድህ፤ አሕዛብን በቍጣ አሄድሃቸው።

13ሕዝብህን ለመታደግ፥ የቀባኸውንም ለማዳን ወጣህ፤ የኃጢአተኛውን ቤት ራስ ቀጠቀጥህ፤ መሠረቱን እስከ አንገቱ ድረስ ገለጥህ።

14የአለቆችን ራስ በገዛ በትራቸው ወጋህ፤ እኔን ይበትኑ ዘንድ እንደ ዐውሎ ነፋስ መጡ፤ ችግረኛውን በስውር ለመዋጥ ደስታቸው ነው።

15ፈረሶችህን በባሕር፥ በብዙ ውኆችም ላይ አስረገጥህ።

16እኔ ሰምቻለሁ፥ ልቤም ደነገጠብኝ፤ ከድምፁ የተነሣ ከንፈሮቼ ተንቀጠቀጡ፤ መንቀጥቀጥ ወደ አጥንቶቼ ውስጥ ገባ፤ በስፍራዬ ሆኜ ተናወጥሁ፤ በሚያስጨንቁን ሕዝብ ላይ እስኪመጣ ድረስ የመከራን ቀን ዝም ብዬ እጠብቃለሁ።

17ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፥ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራ ሥራ ቢጐድል፥ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፥ በጎች ከበረቱ ቢጠፉ፥ ላሞችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ፥

18እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ።

19ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌ ነው፤ እግሮቼን እንደ ዋላ እግሮች ያደርጋል፤ በከፍታዎችም ላይ ያስሄደኛል።

ማብራሪያ

3:1,2 ጸሎት የሚለው ቃል እዚህ ላይ ለአምልኮ ተግባር የተጠቀሰ ይመስላል። እግዚአብሔር በመከራ ዘመን አጋማሽ ላይ በሕዝቡ መካከል ሥራውን ያድሳል። ይህ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ወይም አማኞች በመከራና በፈተና በሚያልፉበት በእያንዳንዱ ወቅት ሊተገበር ይችላል። ምህረት ልንሸሽበት የሚገባን መጠጊያችን፣ እንዲሁም ብቸኛ መማጸኛችን አድርገን የምንታመንበት ነው። ‹ትሩፋታችንን አስብልን› ማለት የለብንም፤ ይልቁንም ‹ጌታ ሆይ፣ የራስህን ምህረት አስብ› ልንል ይገባል።

3:3-15 የእግዚአብሔር ሕዝብ በመከራ ውስጥ ሲሆኑና ተስፋ ለመቁረጥ በተቃረቡ ጊዜ፣ የቀድሞውን ዘመን ቀኖችና የጥንት ዓመታትን በማሰብ፣ እንዲሁም በጸሎት ለእግዚአብሔር በማቅረብ እርዳታ ይሻሉ። በባቢሎንና በግብፅ ምርኮዎች መካከል ያለው ተመሳሳይነት፣ በተፈጥሮአቸው ወደ አእምሮአቸው ይመጣል፤ እንደዚሁም በይሖዋ ኃይል ተመሳሳይ መዳን የመቻል እድልም እንዲሁ። እግዚአብሔር በክብሩ ታየ። የተፈጥሮ ኃይሎች ሁሉ ተናወጡ፣ የተፈጥሮ ሥርዓትም ተለወጠ፤ ነገር ግን ይህ ሁሉ የእግዚአብሔር የራሱ ሕዝብ ለመዳን ነው። እጅግም የማይመስል የሚመስለውም እንኳ ለደኅንነታቸው እንዲሠራ ይደረጋል። በዚህም በኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ቤዛነት ምሳሌና አርአያ ተሰጥቷል። ይህ ከመሲህህ ጋር ለመዳን ነው። የእስራኤልን ሠራዊት የመራው ኢያሱ፣ ስሙን የተሸከመው እርሱ – የኛ ኢያሱ የሆነው ኢየሱስ – ምሳሌ ነበር። ለእነርሱ በተደረጉት መዳኖች ሁሉ፣ እግዚአብሔር የተቀባውን ክርስቶስን ተመለከተ፣ በእርሱም አማካኝነት ነፃ መውጣቶችን አደረገ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6