ትንቢተ ዕንባቆም 1

AMHNIVአማርኛ17 ጥቅሶች3:06 አዳምጥ
አዳምጥ 3:06 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ነቢዩ ዕንባቆም የተቀበለው ንግር፤

2እግዚአብሔር ሆይ፤ ለርዳታ እየተጣራሁ፣ አንተ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? “ግፍ በዛ” ብዬ እየጮኽሁ፣ አንተ የማታድነው እስከ መቼ ነው?

3ስለ ምን በደልን እንዳይ አደረግኸኝ? እንዴትስ ግፍ ሲፈጸም ትታገሣለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ አለ፤ ጠብና ግጭት በዝቶአል።

4ስለዚህ ሕግ ላልቶአል፤ ፍትሕ ድል አይነሣም፤ ፍትሕ ይጣመም ዘንድ፣ ክፉዎች ጻድቃንን ይከባሉ።

5“ቢነገራችሁም እንኳ፣ የማታምኑትን እናንተን፣ በዘመናችሁ አንድ ነገር ስለማደርግ፣ እነሆ፤ ሕዝቡን እዩ፤ ተመልከቱም፤ እጅግም ተደነቁ።

6የራሳቸው ያልሆኑትን መኖሪያ ስፍራዎች ለመያዝ፣ ምድርን ሁሉ የሚወሩትን፣ ጨካኝና ፈጣን የሆኑትን፣ ባቢሎናውያንን አስነሣለሁ።

7እነርሱም የሚያስፈሩና የሚያስደነግጡ ናቸው፤ ፍርዳቸውና ክብራቸው፣ ከራሳቸው ይወጣል።

8ፈረሶቻቸው ከነብር ይልቅ ፈጣኖች፣ ከማታም ተኵላ ይልቅ ጨካኞች ናቸው። ፈረሰኞቻቸው በፍጥነት ይጋልባሉ፤ ከሩቅ ስፍራም ይመጣሉ። ነጥቆ ለመብላት እንደሚቸኵል አሞራ ይበራሉ፤

9ሁሉም ለዐመፅ ታጥቀው ይመጣሉ። ሰራዊታቸው እንደ ምድረ በዳ ነፋስ ወደ ፊት ይገሠግሣል፤ ምርኮኞችንም እንደ አሸዋ ይሰበስባል።

10ነገሥታትን ይንቃል፤ በገዦችም ላይ ያፌዛል፤ በምሽግ ሁሉ ላይ ይሥቃል፤ የዐፈር ቊልል ሠርቶም ይይዘዋል።

11ከዚያም በኋላ እንደ ነፋስ ዐልፎ ይሄዳል፤ ጒልበታቸውን አምላካቸው ያደረጉ በደለኞች ናቸው።

12እግዚአብሔር ሆይ፤ ከዘላለም ጀምሮ ያለህ አይደለህምን? የእኔ አምላክ፣ የእኔ ቅዱስ እኛ አንሞትም፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዲፈርዱ ሾመሃቸዋል፤ ዐለት ሆይ፤ ይቀጡ ዘንድ ሥልጣን ሰጠሃቸው።

13ዐይኖችህ ክፉውን እንዳያዩ እጅግ ንጹሓን ናቸው፤ አንተ በደልን መታገሥ አትችልም፤ ታዲያ፣ አታላዮችን ለምን ትታገሣለህ? ክፉው ከራሱ ይልቅ ጻድቅ የሆነውን ሲውጠውስ፣ ለምን ዝም ትላለህ?

14አንተ ሰዎችን በባሕር ውስጥ እንዳለ ዓሣ፣ ገዥ እንደሌላቸውም የባሕር ፍጥረታት አደረግህ።

15ክፉ ጠላት ሁሉንም በመንጠቆ ያወጣቸዋል፤ በመረቡ ይይዛቸዋል፤ በአሽክላው ውስጥ ይሰበስባቸዋል፤ በዚህም ይደሰታል፤ ሐሤትም ያደርጋል።

16በእነርሱ ተዝናንቶ ይኖራልና፤ ምግቡም ሰብቶአል። ስለዚህ ለመረቡ ይሠዋል፤ ለአሽክላውም ያጥናል።

17ታዲያ መረቡን ባለማቋረጥ መጣል፣ ሕዝቦችንስ ያለ ርኅራኄ መግደል አለበትን?

ማብራሪያ

1:1-11 የጌታ አገልጋዮች ኃጢአተኝነትና ዓመፅ ሲሰፍን በማየታቸው እጅግ ያዝናሉ፤ በተለይም እውነትን በይፋ በሚናገሩት መካከል ሲሆን ነው። ማንም ሰው ጎረቤቱን ክፉ ከመሥራት ወደ ኋላ አላለም። እኛም ቅድስናና ፍቅር ለዘላለም በሚነግሡበት፣ ምንም ዓይነት ዓመፅም በፊታችን የማናይበት ወደዚያ ዓለም ለመሄድ ልንጓጓ ይገባል። እግዚአብሔር ለክፉ ሰዎች ለሚያሳየው ትዕግስት እንዲሁም ለመልካም ሰዎች ለሚያደርገው ተግሣጽ መልካም ምክንያቶች አሉት። ክፉ በሠሩ ሰዎች ላይ የኃጢአት ጩኸት የሚሰማበት፣ በደል የደረሰባቸው ሰዎች ደግሞ የጸሎት ጩኸት የሚሰማበት ቀን ይመጣል። በአሕዛብ መካከል በከለዳውያን አማካኝነት ምን እየተካሄደ እንደሆነ ሊመለከቱ ይገባ ነበር፤ እነሱ ራሳቸውም በእነሱ የሚገረፍ ሕዝብ እንደሆኑ ሊገነዘቡ ይገባ ነበር። አብዛኞቹ ሰዎች ግን ቀጣይነት ባለው ብልጽግና ላይ ይተማመናሉ ወይም መከራዎች በዘመናቸው እንደማይመጡ ያስባሉ። እነሱም መራራና ፈጣን ሕዝብ ናቸው፤ ጨካኞች፣ ግፈኞች እና በፊታቸው ያለውን ሁሉ የሚያደቅቁ ናቸው። የሚቃወሟቸውን ሁሉ ያሸንፋሉ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6