1ቂሮስ የፋርስ ንጉሥ በሆነ በመጀመሪያው ዓመት፣ እግዚአብሔር የቂሮስን መንፈስ አነሣሥቶ በመንግሥቱ ሁሉ ዐዋጅ እንዲያስነግርና ይህም በጽሑፍ እንዲሰፍር አደረገ፤ ይህ የሆነው በኤርምያስ አፍ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።
2“የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ የሚለው ይህ ነው፤ “ ‘የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳ ምድር በምትገኘው በኢየሩሳሌምም ለእርሱ ቤተ መቅደስ እንድሠራ አዞኛል።
3ከሕዝቡ መካከል በእናንተ ዘንድ የሚኖር ማናቸውም ሰው አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፤ በይሁዳ ወደምትገኘው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣና በዚያ ለሚኖረው አምላክ፣ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ይሥራ፤
4ባሉበት ስፍራ የሚቀሩ በየትኛውም አገር የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በኢየሩሳሌም ለሚገኘው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ስጦታ እንዲሆን በበጎ ፈቃድ ከሚያቀርቡት መባ በተጨማሪ ብርና ወርቅ፣ ዕቃና እንስሳ በመስጠት ይርዷቸው።’ ”
5ከዚያም እግዚአብሔር መንፈሳቸውን ያነሣሣው የይሁዳና የብንያም ቤተ ሰብ አለቆች እንዲሁም ካህናቱና ሌዋውያኑ ሁሉ ለመሄድና በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለመሥራት ተዘጋጁ።
6ጎረቤቶቻቸውም ሁሉ በበጎ ፈቃድ ከሰጡት መባ በተጨማሪ ከብርና ከወርቅ የተሠሩ ዕቃዎችን፣ ቈሳቍስን፣ እንስሶችንና ሌሎች ጠቃሚ የሆኑ ስጦታዎችንም በመለገስ ረዷቸው።
7ከዚህም በላይ ንጉሡ ቂሮስ፣ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወስዶ በአማልክቱ ቤተ ጣዖት ያኖራቸውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ንዋያተ ቅድሳት አወጣ።
8የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ በግምጃ ቤቱ ኀላፊ በሚትሪዳጡ አማካይነት ንዋያተ ቅድሳቱ እንዲመጡና በይሁዳው ገዢ በሰሳብሳር ፊት እንዲቈጠሩ አደረገ።
9የዕቃው ዝርዝር ይህ ነበር፤ የወርቅ ሳሕን 30 የብር ሳሕን 1,000 ዝርግ የብር ሳሕን 29
10ጐድጓዳ የወርቅ ሳሕን 30 ባለ ግጣም የብር ጐድጓዳ ሳሕን 410 ሌሎች ቈሳቍስ 1,000
11ባጠቃላይ አምስት ሺህ አራት መቶ የወርቅና የብር ዕቃዎች ነበሩ። ሰሳብሳር ምርኮኞቹ ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሱ ይህን ሁሉ ዕቃ ይዞ ወጣ።