1ጌታ ሰውን ከመሬት ፈጠረ፤ ወደ እርሷም ይመልሰዋል።
2ለሰዎች ብዙ ቀናትንና ጊዜም ሰጣቸው፤ በምድርም በሚገኘው ላይ ሁሉ ሥልጣንን ሰጣቸው።
3እንደ ራሱ ብርታትን አለበሳቸው፤ በአምሳሉ ፈጠራቸው።
4የዱር አውሬዎችና ወፎች እንዲታዘዟቸው፥ የምድር ፍጥረት ሁሉ እንዲፈራቸው አደረገ።
6ምላስን፥ ዓይንና ጆሮን ሠራላቸው፤ የሚያስቡበትንም ልቦና ሰጣቸው።
7በዕውቀትና በማስተዋል ሞላቸው፤ ደግንና ክፉን እንዲለዩ አደረጋቸው።
8የሥራዋቹንም ታላቅነት እንዲያዩ፥ በልባቸውም የራሱን ብርሃን አኖረ።
9ስለ ድንቅ ሥራዎቹ እንዲገሩ፥
10ቅዱሱን ስሙን እንዲያመሰግኑ፥
11ዕውቀትንም በፊታቸው አኖረ፥ የሕይወትንም ሕግ ሰጥቷቸዋል።
12ከነሱ ጋር ዘላለማዊ ቃል ኪዳን ገብቷል፤ ፍርዶቹንም ገልጾላቸዋል።
13ዐይኖቻቸው የክብሩን ታላቅነት አይተዋል፤ ጆዎቻቸው የድምፁን ግርማ ሰምተዋል።
14“ከክፉ ሁሉ ተጠንቀቁ” አላቸው፥ እያንዳንዳቸው ባልንጀሮቻቸውን በተመለከተም ትዕዛዝ ሰጥቷቸዋል።
15መንገዶቻቸው ከእይታው አያመልጡም፤ በዐይኑም ይከታተላቸዋል።
17በእያንዳንዱ ሀገር አስቀምጧል፥ ይሁን እንጂ እስራኤል የእግዚአብሔር ድርሻ ናት።
19ሥራዎቻቸው ሁሉ በሱ ፊት እንደ ፀሐይ ግልጽ ናቸው፤ ዐይኖቹ ሁልጊዜ በባሕሪያቸው ላይ ያነጣጥራሉ።
20ክፋታቸው ከእርሱ አይሰወርም፤ ኃጢአቶቻቸውም በፊቱ ይቀርባሉ።
22ምጽዋት ለእርሱ እንደ ቀለበት ማኀተም ነው፤ በሰው ውስጥ ያለው ደግነት ለልክ እንደ ዐይን ብሌን ያስደስተዋል፤
23አንድ ቀን ተነሥቶ ይሸልማቸዋል፤ ዋጋቸውን ለየራሳቸው ይከፍላቸዋል።
24ነገር ግን ንስሐ ለሚገቡ እንዲመለሱ ይፈቀድላቸዋል፤ ተስፋ የቆረጡትንም ያበረታቸዋል።
25ወደ እግዚአብሔር ተመለስ፥ ኃጢአቶችህንም አውግዝ፥ በፊቱ ለምን፥ እሱንም አታስቀይመው።
26ወደ ልዑል እግዚአብሔር ተመለስ፤ ከክፉ ነገር ራቅ፤ መጥፎውን ሁሉ ጥላ።
27በሕይወት እያለን ከፍ ከፍ ካላደረግነው፥ ሲኦል ወርዶ የሚያመሰግነው ይኖራልን?
28የሞቱትን እንደ ሌሎች ሁሉ ማመስገን አይችሉም፤ እግዚአብሔርን የሚያወድሱ ሕያዋንና ጤነኞች ብቻ ናቸው።
29የእግዚአብሔር ምሕረት ምንኛ ታላቅ ነው፤ ወደሱ ለሚመለሱ ሰዎች ይቅርታው ምንኛ የበዛ ነው።
30የምንሻው ሁሉ ሊኖረን አይችልም፤ ሰዎች ዘላለማዊ አይደለንምና።
31ከፀሐይ የበለጠ ድምቀት ያለው አለን? እንዲያም ሆኖ ግን ይደበዝዛል፥ ሥጋና ደምም ከክፋት በስተቀር የሚያልሙት የለም።
32አምላክ የሰማይ ሠራዊትን ይቆጣጠራል፥ እኛ ግን ትቢያና አመድ ብቻ ነን።