መጽሐፈ ጥበብ 9

ACEDአማርኛ18 ጥቅሶች

1የአባቶቻችን አምላክ፥ የምሕረት ጌታ፥መላውን ዓለም በቃልህ ፈጠርክ፤

2ፍጡራንህንም ይገዛ ዘንድ፥የሰውን ልጅ በጥበብህ ሠራህ፤

3ዓለምን በቅድስና ለመግዛት፥ ፍትሕንም ለመጠበቅ፥በነፍስ ታማኝነት ያልተዛባ ፍርድ ለመስጠት፥

4በዙፋንህ የምትቀመጥ ጥበብን ስጠኝ፤ከልጆችህም መሀል አትነጥለኝ።

5እኔ አገልጋይህ የአገልጋይትህ ልጅ፥ለአጭር ጊዜ የምኖር ደካማ ሰው፥ስለ ሕጎችህና ስለ ፍትሕ የማላውቅ ነኝና።

6አንድ ፍጹም ከሰዎች መካከል ቢኖር እንኳን፥ያንተ የሆነችውን ጥበብ ካላገኘ ቁጥሩ ከከንቱዎች ነው።

7በሕዝቦችህ ላይ እንድነግሥ መረጥኸኝ፤በወንድና በሴት ልጆችህም ላይ እንድፈርድ ፈቀድክ።

8በቅዱሱ ተራራ ላይ ቤተ መቅደስህን እንድገነባ፥ድንኳንህን በተከልክበት ከተማ፥ ጥንት ያዘጋጀሃትን የቀደሰች ድንኳን ዓይነት፥መሠዊያህን እንድሠራ አዘዝከኝ።

9ዓለምን በፈጠርህ ጊዜ ከጐንህ ያልተለየችው፥ሥራዎችህን የምታውቀው ጥበብ ካንተ ጋር ናት።አንተን ደስ የሚያሰኘውን፥ከትእዛዞችህ ጋር የሚስማማውን ሁሉ ታውቃለች።

10እኔን እንድትረዳኝ፥ ከእኔ ጋር እንድትደክም፥አንተን የሚያስደስትህን እንድታስምረኝ፥ከቅዱሳን ሰማያት አውጣት፤ከከበረው ዙፋንህም ወደዚህ ላካት።

11ሁሉንም የምታውቅና የምትረዳ በመሆኗ፥በሥራዎቼ ላይ ሁሉ በጥንቃቄ ትመራኛለች፤ክብሯም ትጠብቀኛለች።

12ያኔ የማደርገው ሁሉ ተቀባይነትን ያገኛል፤ሕዝብህን በትክክል እመራለሁ፤ለአባቴ ዙፋንም የተገባሁ እሆናለሁ።

13የእግዚአብሔርን ሐሳብ ሊያውቅ የሚችል ሰው ማን ነው?የጌታንስ ፈቃድ በውል የሚገነዘብ ማን ነው?

14የሰዎች ግንዛቤ በስህተት የተሞላ ነው፤አመለካከታቸውም ወላዋይ ነው፤

15ፈራሹ ሥጋ ነፍስን ይከብዳታል፥ምድራዊው ድንኳንም የሚያስብ ልቡናን ይጫነዋል።

16በምድር ላይ ያለውን ለማወቅ እንቸገራለን፤ባጠገባችን ያለውንም ለመረዳት እንደክማለን፤እንግዲያውስ በሰማያት ያለውን ሊያውቅ የሚችል ከቶ ማን ነው?

17አንተ ጥበብን ባትሰጥ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ባትልክ ኖሮ፥ማን ፈቅድህን ሊያውቅ ይችል ነበር?

18በዚህ ዓይነት የምድር ነዋሪዎች መንገድ ተቃና፤ሕዝቦች ደስ የሚያሰኝህን ሁሉ ተማሩ፤በጥበብም ዳኑ።

ትርጉሞች1 · 1