መጽሐፈ ጥበብ 10

ACEDአማርኛ21 ጥቅሶች

1የመጀመሪያውን ሰው፥ የዓለምን አባት፥በመልካም ሁኔታ ይቀረጽ ዘንድ፥ከወደቀበት ያዳነችው እርሷ ናት፤

2ሁሉን ይገዛም ዘንድ ኃየልን ሰጠችው።

3ክፉው ሰው በተቆጣ ጊዜ ግን እርሷን ተዋት፤በንዴት ወንደሙን በመግደሉ በጥፋት ላይ ወደቀ።

4በእርሱ ጥፋት መሬት በውሃ በተጥለቀለቀች ጊዜ፥አሁንም ያዳነችው ጥበብ ናት።ጻድቁን ሰው በእንጨት አንሳፋ አዳነችው።

5ሰዎች ክፉ በመፈጸም ሲያድሙ፥ እንዲበጣበጡ ተፈረደባቸው፤ያንጊዜ ጻድቁን ሰው ለየች፤ በእግዚአብሔርም ፊት አቀረበች፤ከልጁም ኀዘን አበረታችው።

6ክፉዎች በጠፉ ጊዜ ጻድቁን ያዳነች እርሷ ናት፤ስለ ክፋታቸው ምስክር ይሆን ዘንድ፥ ከነደደው መሬት፥

7ተክሎች የማይበስል ፍሬ ከተሸከሙበት፥ላላመነች ነፍስ የቆመው መታሰቢያ የጨው ዓምድ ሆኖ ከቀረበት፥በአምስቱ ከተሞች ላይ ከወረደው እሳት ሸሽቶ እንዲያመልጥ ረድታዋለች።

8የጥበብን መንገድ ባለመሻት፥ ጥሩውን ለማወቅ ካለመቻላቸው በላይየስሕተታቸውን መታሰቢያ ጥለው አልፈዋል፤በዚህም ገበናቸውን ሁሉም ያየዋል።

9ጥበብ ግን አገልጋዮቿን ሁሉ፥ ከመከራ ታደገቻቸው።

10ከወንድሙ ቁጣ የሚሸሸውን ጻድቅ ሰው፥በቀና መንገዶች መራችው፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት አሳየችው፤ስለ ቅዱስ ነገሮችም ያውቅ ዘንድ አስተማረችው፤ድካሙ ፍሬ እንዲያፈራ አደረገች፤ የጥረቱንም ዋጋ ሰጠችው።

11ከጨቋኞችና ከስግብግቦች ጋር ስፋለም፥ ከጐኑ ቆመች፤ባለጸጋም አደረገችው።

12ከጠላቶቹ ጠበቀችው፤ ካጠመዱበትም ወጥመድ አወጣችው።በመራራዉ የትግል ወቅት ሸለመችው።የተቀደሰ ተግባር ከሁሉም በላይ መሆኑን አስተማረችው።

13በተሸጠ ጊዜ ከጻድቁ ሰው አልራቀችም፤ከኃጢአትም መንጥቃ አወጣችው።

14ከጉድጓድ ውስጥ አብራው ገባች፤በሰንሰለት በታሰረ ጊዜ አልተወችውም፤በትረ መንግሥቱን እስኪጨብጥ፥ በጨቋኞችም ላይ ሥልጣንን እስኪያገኝ፥ ከጐኑ አልጠፋችም።በውሸት ያሙትን ሁሉ፥ ሐሰተኞች እንደ ሆኑ አግልጣለች፤ዘላለማዊ ክብርንም አጐናጽፋዋለች።

15ንጹሕ ዘር የሆነውን የቀደሰ ሕዝብ፥ከጨቋኞች መዳፍ የታደገችው ጥበብ ነች።

16በጌታ አገልጋይ ነፍስ ውስጥ ዘልቃ፥በታምራትና በምልክቶች አስፈሪ ነገሥታትን የተቋቋመች ጥበብ ናት።

17ለተቀደሱ ሰዎች የልፋታቸውን ዋጋ ከፍላለች፤በአስደናቂ መንገድም መራቻቸው፤ በቀን ተገን፤በሌሊት የኮከብ ብርሃን ሆነችላቸው።

18ቀይ ባሕርን አሻገረቻቸው፤ በግዙፍ የውሃ አካልም ውስጥ መራቻቸው፤

19ጠላቶቻቸውን ግን አስመጠች፤ ኋላም ከጥልቁ ጉድጓድ ተፋቻቸው።

20ስለዚህ ጻድቃን ክፉዎቹን በረበሯቸው፤ጌታ ሆይ የተቀደሰውን ስምህንም አመስግኑ፤በአንድነት ጠባቂ ክንድህን አወድሱ፤

21ጥበብ የዱዳዎችን አንደበት ከፍታለች፤የሕፃናትንም ምላስ ፈትታለችና።

ትርጉሞች1 · 1