1ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የራሱን ቤተ መንግሥት የሠራባቸው ሃያ ዓመት ከተፈጸመ በኋላ፣
2ኪራም የሰጠውን ከተሞች አድሶ እስራኤላውያን እንዲሰፍሩባቸው አደረገ።
3ከዚያም ሰሎሞን ወደ ሐማት ሱባ ዘመተ፤ ያዛትም።
4በምድረ በዳውም ውስጥ ተድሞርንና ቀድሞ በሐማት ሠርቶአቸው የነበሩትን የዕቃ ቤት ከተሞች ሁሉ ሠራ።
5እንዲሁም የላይኛውን ቤትሖሮንና የታችኛውን ቤትሖሮን የተመሸጉ ከተሞች አድርጎ ከቅጥሮቻቸው፣ ከበሮቻቸውና ከመዝጊያዎቻቸው ጋር ሠራ።
6ደግሞም ባዕላትንና የዕቃ ቤት ከተሞቹን ሁሉ፣ ሠረገሎችና ፈረሶች የሚኖሩባቸውን ከተሞች ሁሉ፣ ባጠቃላይ በኢየሩሳሌም፣ በሊባኖስና በግዛቱ ሁሉ ለመሥራት የፈለጋቸውን ነገሮች ሁሉ ሠራ።
7እስራኤላውያን ያልሆኑ ግን ከኬጢያውያን፣ ከአሞራውያን፣ ከፌርዜያውያን፣ ከኤዊያውያንና ከኢያቡሳውያን የቀሩት ሕዝቦች ሁሉ፣
8እስራኤላውያን ያላጠፏቸውን፣ በምድሪቱ የቀሩ ዘሮቻቸውን የጒልበት ሥራ ይሠሩ ዘንድ ሰሎሞን መለመላቸው፤ እስከ ዛሬም ይሠራሉ።
9ይሁን እንጂ ሰሎሞን ማንም እስራኤላዊ ባሪያ ሆኖ በግዳጅ ሥራውን እንዲሠራ አላደረገም፤ እነርሱ ተዋጊዎች፣ የሻምበል አዛዦች፣ የሠረገሎችና የሠረገላ ነጂዎች አዛዦች ነበሩና።
10ከእነዚህም ሁለት መቶ አምሳዎቹ የንጉሥ ሰሎሞን ሹማምት ሰዎቹን የሚቈጣጠሩ ነበሩ።
11ሰሎሞንም፣ “የእግዚአብሔር ታቦት የገባበት ቦታ ሁሉ ቅዱስ ስለ ሆነ፣ ሚስቴ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት ቤተ መንግሥት መኖር አይገባትም” በማለት የፈርዖንን ልጅ ከዳዊት ከተማ እርሱ ወደሠራላት ቤተ መንግሥት አመጣት።
12ሰሎሞንም በቤተ መቅደሱ መመላለሻ ፊት ለፊት ባሠራው የእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረበ።
13ሙሴ ስለ መሥዋዕት አቀራረብ ባዘዘው መሠረት በእያንዳንዱ የበዓል ቀን ይኸውም በየሰንበቱ፣ በየወሩ መባቻና በሦስቱ የዓመት በዓላት ማለትም በቂጣ በዓል፣ በመከር በዓልና በዳስ በዓል ጊዜ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረበ።
14የአባቱን የዳዊትን ሥርዐት በመከተልም፣ ካህናቱን በየአገልግሎት ክፍላቸው ሌዋውያኑንም ምስጋናውን እንዲመሩና በየዕለቱ ሥራቸው ካህናቱን እንዲረዱ መደባቸው። ደግሞም የእግዚአብሔር ሰው ዳዊት ባዘዘው መሠረት የቤተ መቅደሱን በር ጠባቂዎች በልዩ ልዩ በሮች ጥበቃ ላይ በየክፍላቸው መደባቸው።
15እነርሱም ንጉሡ ግምጃ ቤቱን ጨምሮ ስለማናቸውም ነገር ለካህናቱና ለሌዋውያኑ የሰጠውን ትእዛዝ አልተላለፉም ነበር።
16የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠረት ከተጣለበት ዕለት አንሥቶ እስከ ፍጻሜው ድረስ ያለው የሰሎሞን ሥራ ሁሉ ተከናወነለት፤ በዚሁ ሁኔታም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥራ ከፍጻሜ ደረሰ።
17ከዚያም ሰሎሞን የኤዶም የባሕር ጠረፍ ወደሆኑት ወደ ዔዮንጋብርና ወደ ኤሎት ሄደ።
18ኪራምም ባሕሩን በሚያውቁት በራሱ መኮንኖች የሚታዘዙ መርከቦችን ላከለት፤ እነዚህም ከሰሎሞን ሰዎች ጋር በመሆን ወደ ኦፊር ተጓዙ፤ ከዚያም አራት መቶ አምሳ መክሊት ወርቅ አምጥተው ለንጉሥ ሰሎሞን ሰጡት።