1ኛ ዜና መዋዕል 26

AMHNIVአማርኛ32 ጥቅሶች6:27 አዳምጥ
አዳምጥ 6:27 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1የቤተ መቅደሱ በር ጠባቂዎች አመዳደብ፤ ከቆሬያውያን ወገን፤ ከአሳፍ ወንዶች ልጆች አንዱ የሆነው የቆሬ ወንድ ልጅ ሜሱላም።

2ሜሱላም ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ የመጀመሪያው ዘካሪያስ፣ ሁለተኛው ይዲኤል፣ ሦስተኛው ዮዛባት፣ አራተኛው የትኒኤል፣

3አምስተኛው ኤላም፣ ስድስተኛው ይሆሐናን፣ ሰባተኛው ኤሊሆዔናይ።

4ዖቤድኤዶምም እንደዚሁ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ የመጀመሪያው ሸማያ፣ ሁለተኛው ዮዛባት፣ ሦስተኛው ኢዮአስ፣ አራተኛው ሣካር፣ አምስተኛው ናትናኤል፣

5ስድስተኛው ዓሚኤል፣ ሰባተኛው ይሳኮር፣ ስምንተኛው ፒላቲ፤ እግዚአብሔር ዖቤድኤዶምን ባርኮታልና።

6እንዲሁም ልጁ ሸማያ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም በቂ ችሎታ ስለ ነበራቸው የአባታቸው ቤት መሪዎች ሆነው ነበር።

7የሽማያ ወንዶች ልጆች፤ ዖትኒ፣ ራፋኤል፣ ዖቤድ፣ ኤልዛባድ፤ ዘመዶቹ ኤሊሁና ሰማክያም እንደዚሁ በቂ ችሎታ ነበራቸው።

8እነዚህ ሁሉ የዖቤድኤዶም ዘሮች ሲሆኑ፣ እነርሱም ሆኑ ወንዶች ልጆቻቸውና ቤተ ዘመዶቻቸው ሥራውን ለመሥራት በቂ ችሎታ ነበራቸው። የዖቤድኤዶም ዘሮች ባጠቃላይ ሥልሳ ሁለት ነበሩ።

9ሜሱላም በቂ ችሎታ ያላቸው ወንዶች ልጆችና ቤተ ዘመዶች ነበሩት፤ ቊጥራቸውም ባጠቃላይ ዐሥራ ስምንት ነበረ።

10ከሜራሪ ወገን የሆነው ሖሳ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ የመጀመሪያው ሽምሪ ነበረ፤ የበኵር ልጅ ባይሆንም እንኳ፣ አባቱ ቀዳሚ አድርጎት ነበር።

11ሁለተኛው ኬልቅያስ፣ ሦስተኛው ጥበልያ፣ አራተኛው ዘካርያስ፤ የሖሳ ወንዶች ልጆችና ቤተ ዘመዶቹ ባጠቃላይ ዐሥራ ሦስት ነበሩ።

12የቤተ መቅደሱም ጠባቂዎች በአለቆቻቸው ሥር ተመድበው ልክ እንደ ቤተ ዘመዶቻቸው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሥራ ለማከናወን ምድብ ተራ ነበራቸው።

13ለእያንዳንዱም በር ወጣት ሽማግሌ ሳይባል ለሁሉም እኩል ዕጣ ተጣለ።

14የምሥራቁ በር ዕጣ ለሴሌምያ ወጣ። ከዚያም ምክር ዐዋቂ ለሆነው ለልጁ ለዘካርያስ ዕጣ ጣሉ፤ እርሱም የሰሜኑ በር ደረሰው።

15የደቡቡ በር ዕጣ ለዖቤድኤዶም ሲወጣ፣ የግምጃ ቤቱ ዕጣ ደግሞ ለልጆቹ ወጣ።

16የምዕራቡ በርና በላይኛው መንገድ ላይ የሚገኘው የሸሌኬት በር ዕጣዎች ለሰፊንና ለሖሳ ወጣ።

17በአንዱ ዘብ ጥበቃ ትይዩ ሌላ ዘብ ጥበቃ ነበረ፤ በየቀኑም በምሥራቅ በኩል ስድስት፣ በሰሜን በኩል አራት፣ በደቡብ በኩል አራት፣ በዕቃ ቤቱ በኩል በአንድ ጊዜ ሁለት ሌዋውያን ይጠብቁ ነበር።

18በምዕራቡ በኩል የሚገኘውን አደባባይ ደግሞ በመንገዱ ላይ አራት፣ በአደባባዩ ላይ ደግሞ ሁለት ሆነው ይጠብቁ ነበር።

19እንግዲህ የቆሬና የሜራሪ ዘሮች የሆኑት በር ጠባቂዎች ድልድል ይህ ነበር።

20ከሌዋውያን መካከል አኪያ የእግዚአብሔር ቤት ግምጃ ቤትና የተቀደሱት ዕቃዎች የሚቀመጡበት ግምጃ ቤት ኀላፊ ነበረ።

21የለአዳን ዘሮች፣ በለኣዳን በኩል ጌድሶናውያን የሆኑትና ለጌድሶናዊው ለለአዳን ቤተ ሰቦች አለቆች የሆኑት የለአዳን ዘሮች እነዚህ ነበሩ፤ ይሒኤሊ፣

22የይሒኤሊ ወንዶች ልጆች፣ ዜቶምና ወንድሙ ኢዩኤል። እነዚህም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግምጃ ቤት ኀላፊዎች ነበሩ።

23ከእንበረማውያን፣ ከይስዓራውያን፣ ከኬብሮናውያን፣ ከዑዝኤላውያን፤

24የሙሴ ልጅ የጌርሳም ዘር የሆነው ሱባኤል የግምጃ ቤቱ የበላይ ኀላፊ ነበረ።

25በአልዓዛር በኩል የሚዛመዱት፤ ልጁ ረዓብያ፣ ልጁ የሻያ፣ ልጁ ኢዮራም፣ ልጁ ዝክሪ፣ ልጁ ሰሎሚት።

26ሰሎሚትና የሥጋ ዘመዶቹ ንጉሥ ዳዊት፣ የቤተ ሰቡ ኀላፊዎች፣ የሻለቆችና የመቶ አለቆች እንዲሁም ሌሎች የሰራዊቱ አዛዦች ቀድሰው ላቀረቧቸው ንዋያተ ቅድሳት ኀላፊዎች ነበሩ።

27በጦርነት ከተገኘውም ምርኮ ከፊሉን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ማደሻ እንዲሆን ቀደሱት።

28ባለ ራእዩ ሳሙኤል፣ የቂስ ልጅ ሳኦል፣ የኔር ልጅ አበኔር፣ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የቀደሱትን ሁሉና እንዲሁም ሌሎቹን ንዋያተ ቅድሳት ሰሎሚናትና ቤተ ዘመዶቹ ይጠብቁ ነበር።

29ከይስዓራውያን፤ ከናንያና ወንዶች ልጆቹ ከቤተ መቅደሱ ውጭ ባለው ሥራ በእስራኤል ላይ ሹማምትና ዳኞች ሆነው ተመደቡ።

30ከኬብሮናውያን፤ ሐሽብያ፣ ጠንካራና ጐበዝ የሆኑ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሰዎች ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ በሚገኘው የእስራኤል ምድር ላለው የእግዚአብሔር ሥራና ለንጉሡም አገልግሎት ኀላፊዎች ሆነው ተመደቡ።

31በኬብሮናውያን በኩል በቤተ ሰቦቻቸው የትውልድ መዝገብ መሠረት ይሪያ አለቃቸው ነበረ። በዳዊት ዘመነ መንግሥት በአርባኛው ዓመት መዛግብቱ ተመርምረው ስለ ነበር፣ በገለዓድ ውስጥ ኢያዜር በተባለ ቦታ ከኬብሮናውያን መካከል ጠንካራ ሰዎች ሊገኙ ችለዋል።

32ይሪያም ጠንካሮችና የቤተ ሰባቸው አለቆች የሆኑ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ሥጋ ዘመዶች ነበሩት። ንጉሥ ዳዊትም እነዚህን የእግዚአብሔር ለሆነውና የንጉሡም በሆነው ጒዳይ ላይ ሮቤልን፣ ጋድንና የምናሴን ነገድ እኵሌታ ኀላፊ አድርጎ ሾማቸው።

ማብራሪያ

26:1-32 የሌዋውያን አገልግሎቶች። የቤተ መቅደሱ በረኞችና የግምጃ ቤት ጠባቂዎች፣ መቅደሱን ያለአግባብ ለመግባት የሚሞክሩትን ለመቃወም እንዲሁም የተቀደሱትን ሀብቶች ለመጠበቅ ኃይልና ድፍረት ያስፈልጋቸው ነበር። በየቀኑ በመሠዊያው ላይ እጅግ ብዙ ነገር ይቀርብ ነበር፤ ዱቄት፣ ወይን፣ ዘይት፣ ጨው፣ የማገዶ እንጨት ከመብራቶቹም በተጨማሪ ነበሩ። ከእነዚህም ውስጥ ብዛት ያላቸው አስቀድሞ ይቀመጡ ነበር፤ ከቅዱሳን ልብሶችና ዕቃዎችም በተጨማሪ። እነዚህ የእግዚአብሔር ቤት ሀብቶች ነበሩ። እነዚህ ሀብቶች በሰማያዊ አባታችን ቤት የሚገኘውን ብዛትና እጅግ የሚበቃ፣ ከልክ በላይ የሚትረፈረፍ ሀብትን ምሳሌ ሆነው ያመለክታሉ። ከእነዚያ የተቀደሱ ግምጃ ቤቶች፣ የክርስቶስ የማይመረመር ሀብት፣ ሁሉም ፍላጎቶቻችን ሙሉ በሙሉ ይሟላሉ፤ ከእርሱም ሙላት ተቀብለን፣ ክብሩን ለእርሱ መስጠት አለብን፣ እንዲሁም ችሎታዎቻችንንና ንብረቶቻችንን እንደ ፈቃዱ እንድንጠቀም መጣር አለብን። እንደ ባለሥልጣናትና ዳኞች ሆነው ስለተሾሙት ሰዎች ዘገባ አለን። የመንግሥት ሥልጣን እንደ ክህነት አገልግሎት ሁሉ፣ ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም የእግዚአብሔር ሥርዓት ነውና ቸል ሊባል አይገባም። በመቅደስ አገልግሎት ላይ ከተሰማሩት ሌዋውያን መካከል አንዳቸውም፣ ከዘማሪዎቹም ሆነ ከበረኞቹ አንዳቸውም ቢሆኑ፣ በዚህ ውጫዊ ጉዳይ ላይ አልተሳተፉም ነበር፤ አንድ አገልግሎት ሙሉውን ሰው ለመጠቅለል በቂ ነበርና። ጥበብ፣ ድፍረት፣ የጽኑ እምነት ጥንካሬ፣ ቅዱስ ስሜቶች እና ግዴታችንን በመወጣት የልብ ጽናት ለእያንዳንዱ አገልግሎት አስፈላጊ ወይም ጠቃሚ ናቸው።

ምዕራፍ 26 የሌዋውያን ሥራ እዚህ ላይ ተገልጿል። ያ ነገድ በዳኞች ዘመን ሁሉ፣ ኤሊና ሳሙኤል እስኪገለጡ ድረስ፣ እምብዛም ጉልህ ሚና አልነበረውም። ዳዊት ግን ሃይማኖትን ባነቃቃ ጊዜ፣ ሌዋውያን ከሁሉም ሰዎች ይልቅ ታላቅ ክብር አገኙ። ለነገዳቸው ክብር የሚመጥኑ አስተዋይ ሌዋውያን መኖራቸውም መልካም ነበር። እዚህ ላይ የሚከተሉትን እናገኛለን፦ I. በረኞች ሆነው የተሾሙ ሌዋውያን (ቁ. 1–19)። II. ግምጃ ቤቶችና መጋዘን ጠባቂዎች ሆነው የተሾሙ (ቁ. 20–28)። III. በአገር ውስጥ መኮንኖችና ዳኞች የነበሩ፣ እንዲሁም የሕዝብ ጉዳዮችን የማስተዳደር ኃላፊነት የተሰጣቸው (ቁ. 29–32)።

ቁጥር 1-19 ልብ በሉ፣ I. ቤተ መቅደሱን የሚያገለግሉ በረኞች ተሹመው ነበር። እነዚህም ወደ ቤተ መቅደሱ የሚወስዱትን መንገዶች ሁሉ ይጠብቁ ነበር፤ የውጭ በሮችን ሁሉ ይከፍቱና ይዘጉ ነበር፤ እንዲሁም በሮች ላይ ይቆሙ ነበር። ይህን የሚያደርጉት ለክብር ብቻ ሳይሆን ለአገልግሎትም ነበር፤ በቅድስናው አደባባዮች ውስጥ ሊሰግዱ የሚሄዱትን ሰዎች ሊጠብቁት ስለሚገባው ሥርዓት ለመምራትና ለማስተማር፣ ፈሪዎችን ለማበረታታት፣ እንግዳዎችንና ንጹሕ ያልሆኑትን ለመመለስ፣ እንዲሁም ሌቦችንና የእግዚአብሔርን ቤት ጠላቶች ለመከላከል ነበር። ይህን አገልግሎት በማመሳሰል፣ ለሰማይ መንግሥት መክፈቻ ቁልፎች ለካህናት እንደተሰጡ ይነገራል (ማቴዎስ 16:19)፤ ይህም በክርስቶስ ሕግ መሠረት እንዲያስገቡና እንዲያስወጡ ነው።

II. ለዚህ አገልግሎት ከተጠሩት መካከል አንዳንዶቹ ኃያላን ጀግኖች (ቁ. 6)፣ ብርቱዎች (ቁ. 7)፣ ብቃት ያላቸው ሰዎች (ቁ. 8) እንደነበሩ ተጠቅሷል። ከእነርሱም አንዱ አስተዋይ አማካሪ እንደነበረ (ቁ. 14) ተገልጿል፤ እርሱም ምናልባት የዲያቆንነትን አገልግሎት በሚገባ ካከናወነና ከተለመደው በላይ ጥበብን ካሳየ በኋላ፣ ለራሱ መልካም ማዕረግ አግኝቶ ከበር ጠባቂነት ወደ ምክር ቤት ከፍ ብሎ ሊሆን ይችላል (1 ጢሞቴዎስ 3:13)። በሰውነት ጥንካሬ፣ በድፍረትና በአእምሮ ጽናት የላቁ ሰዎች ለተመደቡበት ቦታ ብቁ ነበሩ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሰዎችን ለየትኛውም አገልግሎት ሲጠራቸው፣ ወይ ብቁ ሆነው ያገኛቸዋል ወይም ብቁ ያደርጋቸዋል።

III. የዖቤድኤዶም ልጆች በዚህ አገልግሎት ተቀጥረው ነበር፤ ከቤተሰቡ ስልሳ ሁለት ሰዎች ነበሩ። እርሱም ታቦቱን በአክብሮትና በደስታ የተቀበለ ሰው ነበር፤ ለዚህም እንዴት እንደተከፈለ ተመልከቱ። 1. እግዚአብሔር ስለባረከው ስምንት ወንዶች ልጆች ነበሩት (ቁ. 5)። የቤተሰቦች መጨመርና መገንባት የእግዚአብሔር በረከት ውጤት ነው፤ እንደነዚህ ያሉ ልጆች ለእግዚአብሔር አገልግሎት ብቁና ታዋቂ ሲሆኑ፣ ብዙ ልጆች መውለድ ለቤተሰብ ታላቅ በረከት ነው። 2. ልጆቹ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ወደ እምነት ቦታዎች ከፍ ከፍ አሉ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6