1ከዚህ በኋላ ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ድል መትቶ ተገዥ አደረጋቸው፤ ጌትንና በዙሪያዋም የሚገኙትን መንደሮች ከፍልስጥኤማውያን እጅ ወሰደ።
2እንዲሁም ዳዊት ሞዓባውያንን ድል አደረጋቸው፤ እነርሱም ገባሮቹ ሆኑ፤ ግብርም አመጡለት።
3ከዚህም በላይ ዳዊት በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ የነበረውን ግዛት ለመቈጣጠር በሄደ ጊዜ፣ የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን እስከ ሐማት ድረስ ዘልቆ ወጋው።
4ዳዊትም አንድ ሺህ ሠረገላ፣ ሰባት ሺህ ፈረሰኛና ሃያ ሺህ እግረኛ ወታደር ማረከ፤ አንድ መቶ የሠረገላ ፈረሶች ብቻ አስቀርቶ የቀሩትን ቋንጃቸውን ቈረጠ።
5ሶርያውያንም የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን ለመርዳት ከደማስቆ በመጡ ጊዜ፣ ከእነርሱ ሃያ ሁለት ሺህ ሰው ገደለ።
6ከዚያም በሶርያ ግዛት ውስጥ ባለችው በደማስቆ የጦር ሰፈር አቋቋመ፤ ሶርያውያን ገባሮቹ ሆኑ፤ ግብርም አመጡለት። እግዚአብሔርም ዳዊትን በሄደበት ሁሉ ድል አጐናጸፈው።
7ዳዊትም የአድርአዛር ጦር አለቆች ያነገቡትን የወርቅ ጋሻ ወሰደ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም አመጣው።
8ዳዊት ከአድርአዛር ከተሞች ከጢብሐትና ከኩን እጅግ ብዙ ናስ ወሰደ፤ ሰሎሞን የናሱን ባሕር፣ ዐምዶቹንና ልዩ ልዩ የናስ ዕቃዎቹን የሠራው በዚሁ ነበር።
9የሐማት ንጉሥ ቶዑ ዳዊት የሱባን ንጉሥ የአድርአዛርን ሰራዊት ሁሉ ድል እንደመታ ሲሰማ፣
10እጅ እንዲነሣውና ደስታውንም እንዲገልጥለት ልጁን አዳራምን ወደ ንጉሥ ዳዊት ላከው፤ ቶዑ ከአድርአዛር ጋር ብዙ ጊዜ ጦርነት ገጥሞ ነበር። አዶራምም ከወርቅ፣ ከብርና ከናስ የተሠሩ ልዩ ልዩ ዕቃዎች አመጣለት።
11ንጉሥ ዳዊት ከኤዶም፣ ከሞዓብ፣ ከአሞናውያን፣ ከፍልስጥኤማውያንና ከአማሌቃውያን ከእነዚህ ሁሉ መንግሥታት የማረከውን ወርቅና ብር ከዚህ ቀደም እንዳደረገው ሁሉ፣ እነዚህንም ዕቃዎች ለእግዚአብሔር ቀደሰ።
12የጽሩያ ልጅ አቢሳ በጨው ሸለቆ ዐሥራ ስምንት ሺህ ኤዶማውያን ገደለ።
13እርሱም በኤዶም የጦር ሰፈሮች አቋቋመ፤ ኤዶማውያንም ሁሉ ለንጉሥ ዳዊት ገባሮች ሆኑ። እግዚአብሔርም ዳዊትን በሄደበት ሁሉ ድል አጐናጸፈው።
14ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ ነገሠ፤ ለሕዝቡም ሁሉ ፍትሕንና ጽድቅን አሰፈነላቸው።
15የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የሰራዊቱ አዛዥ ነበረ፤ የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ ደግሞ የቤተ መዛግብቱ ኀላፊ ነበረ።
16የአኪጦብ ልጅ ሳዶቅና የአቤሜሌክ ልጅ አብያታር ካህናት ነበሩ፤ ሱሳ ደግሞ ጸሓፊ ነበረ።
17የዮዳሄ ልጅ በናያስ የከሊታውያንና የፈሊታውያን አዛዥ ነበረ። የዳዊት ወንዶች ልጆቹ ደግሞ ከንጉሡ ቀጥሎ የበላይ ሹማምት ነበሩ።